ደርግ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ደርግ ከሰኔ 21፣ 1966 እስከ 1983ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰፍኖ የነበር የወታደራዊ አገዛዝ ስርዓት አይነት ነበር። ደርግ የሚለው ቃል ከግዕዝ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ቡድን ወይንም ኮሚቴ ማለት ነው። ይህን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ለስርዓቱ መገለጫነት የተጠቀመው ግለሰብ ሻለቃ ናደው ዘካሪያስ ሲባል ይሄውም ሰኔ 21፣ 1966 ዓ.ም. ነበር[1]። በዚህ ወቅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የአራተኛ እግረኛ ክፍለ ጦር መምሪያ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መለዮ ለባሾች በየካቲት ወር ስለፈነዳው አብዮት ከሰኔ 19 ጀምሮ ውይይት የሚያካሂዱበት ጊዜ የነበር ሲሆን፤ ሻለቃ ናደው የዚህ ኮሚቴ ማስታወቂያ ጉዳይ ሠራተኛ ነበር። ደርግ በዚህ ሁኔታ በዝቅተኛ መኮንኖች (ከኮሎኔል ማዕረግ በታች) ከተመሰረተ በኋላ በዚያው ቀን ሻለቃ መንግስቱ ኃይለማርያም የደርግ ሊቀመንበር በመሆን ተመርጦ እስከ ስርዓቱ ማብቂያ (1979) ድረስ በዚያ ስልጣን አገልግሏል።
°