ራዲዮ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ራዲዮ ራዲዮ ሞገዶችን በመከርከም መልዕክት ከቦታ ቦታ የሚተላለፍበት ቴክኖሎጂ ነው። [1] ራዲዮ ሞገድ የብርሃን አይነት ሞገድ ሲሆን ልዩነቱ የራዲዩ ሞገድ የብርሃንን ያኽል አይርገበገብም። የራዲዮ ሞገድ በአየርም ሆነ በወና ውስጥ የሚጓዘው የኤሌክትሪክ መስኩን በማርገብገብና ሞገድ በመፍጠር ነው። ይህን ሞገድ ባህርዩን በዘዴ በመቀየር (በመከርከም) መልዕክት እንዲያዝል ተደርጎ ይላካል። ለምሳሌ የራዲዮ ሞገዱን ቁመት በአንድ ድምፅ ሞገድ ትክክል ተከርክሞ ሲጫን ኤ.ኤም ራዲዮ ይፈጠራል። በራዲዮ ሞገዱ ድግግሞሽ ላይ ሲጫን ደግሞኤፍ.ኤም ራዲዮ ይሆናል። በሞገዱ ቅድመት ላይ ሊጫን ይችላል፣ ሆኖም ይሄ ብዙ ጊዜ የተለመደ አይደለም። በድምፅ ሞገድ ትክክል የተከረከመው የራዲዮ ሞገድ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ቁስ ሲያጋጥመው በቁሱ ውስጥ ተለዋዋጭ የኤሌክትሪክ ጅረት ይፈጥራል። ይህን ተለዋዋጭ ጅረት የሚተረጉሙ መሳሪያወች የተጫነውን ድምፅ ከራዲዩ ሞገዱ አውርደው ወደ ስፒከሩ በመላክ የራዲዮ ዝግጅት እንዲደመጥ ይሆናል። ከድምፅ በተጨማሪ የምስል መልዕክትም ሊላክ ይችላል፣ በዚህ ወቅት የቴሌቪዥን ዝግጅት እንዲታይ ይሆናል።