ጊዜ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ጊዜ ኩነቶችን (ክስተቶችን) ለመደርደር፣ ቆይታቸውን ለማነጻጻር፣ በመካከላቸውም ያለፈውን ቆይታ ለመወሰን በተረፈም የነገሮችን እንቅስቃሴ መጠን ለመለካት የሚያገለግል ነገር ነው። ጊዜ በፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ሳይንስ ውስጥ ብዙ ጥናት የተካሄደበት ጽንሰ ሃሳብ ቢሆንም ቅሉ እስካሁን ድረስ በሁሉ ቦታ ለሁሉ የሚሰራ ትርጓሜ አልተገኘለትም።
የጊዜ መተግበሪያ ትርጉም ለዕለት ተለት ኑሮ ጠቃሚነቱ ስለታመነበት ከዘመናት በፊት ጀምሮ እስካሁን ይሰራበታል። ይህ መተግበሪያ ትርጉም ለምሳሌ ሰከንድን በመተርጎም ይጀምራል። ማለት በቋሚ ድግግሞሽ የሚፈጠሩ ኩነቶችን/ክስተቶችን በማስተዋል የተወሰነ ድግግማቸውን አንድ ሰከንድ ነው ብሎ በማወጅ የመተግበሪያ ትርጉሙ (ለስራ የሚያመች ትርጉሙ) ይነሳል። ለምሳሌ የልብ ተደጋጋሚ ምት፣ የፔንዱለም ውዝዋዜ ወይም ደግሞ የቀኑ መሽቶ-ነግቶ-መምሸት ወዘተ.. እነዚህ ኩነቶች እራሳቸውን በቋሚነት ስለሚደጋግሙ ከነሱ በመነሳት ሰዓትንና ደቂቃን ማወጅ ይቻላል (መሽቶ ሲነጋ 24 ሰዓት ነው፣ ልብ ሲመታ ወይም ፔንዱለም አንድ ጊዜ ሄዶ ሲመለስ አንድ ሰኮንድ ነው፣ ወዘተ..) ። የመተግበሪያ ትርጉሙ ተግባራዊ ጥቅም ይኑረው እንጂ «ጊዜ በራሱ ምንድን ነው?» ፣ ወይም ደግሞ «ጊዜ አለ ወይ?» ወይም ደግሞ «ጊዜ የሚባል ነገር በራሱ አለ ወይ?» ለሚሉት ጥያቄወች መልስ አይሰጥም።
በአሁኑ ወቅት ጊዜ በሁለት አይነት መንገድ ይታያል፦
- 1. አንደኛው አስተሳሰብ ጊዜ ማለት የውኑ አለም መሰረታዊ ክፍል ሲሆን፣ ማንኛውም ኩነት (event) የሚፈጠርበት ቅጥ ነው። እንግሊዛዊው ሳይንቲስት ኢሳቅ ኒውተን ይህን አስተያየት ስለደገፈ ኒውተናዊ ጊዜ ተብሎ ይታወቃል [1][2] ጊዜ እንግዲህ ባዶ አቃፊ ነገር ሲሆን ኩነቶች በዚህ ባዶ አቃፊ ነገር ውስጥ ይደረደራሉ ማለት ነው። መስተዋል ያለበት ይህ ጊዜ የተባለው አቃፊ ነገር ኩነቶች ኖሩ አልኖሩ ምንግዜም ህልው ነው።
- 2. ከላይ የተጠቀሰውን የጊዜ ጽንሰ ሃሳብ የሚቃወም አስተያየት ሁለተኛው አስተያየት ሲሆን ማንኛውንም አይነት «አቃፊ» የተባለ የጊዜ ትርጉምን ይክዳል፣ እንዲሁም ቁስ አካሎች በዚህ «ጊዜ» በሚባል አቃፊ ነገር ውስጥ መንቀሳቀሳቸውን ይክዳል፣ የጊዜ ፍሰት አለ የሚለውን አስተሳሰብንም ያወጋዛል። ይልቁኑ በዚ በሁለተኛው አስተያየት ጊዜ ማለት አእምሮአችን የውኑን አለም ለመረዳት ከፈጠራቸው ህንጻወች (ቁጥርንና ኅዋን ጨምሮ) አንዱ ሲሆን ሰወች ኩኔቶችን ለመደረደር እና ለማነጻጸር የሚረዳቸው ምናባዊ መዋቅር ነው ይላል። ይህን ሃሳብ ካንጸባረቁት ውስጥ ሌብኒትዝና [3]ካንት,[4][5] ይገኙበታል። ካንት እንዳስተዋለ፦ ጊዜ ማለት ኩኔትም ሆነ ነገር አይደለም ስለዚህም ጊዜን መለካትም ሆነ በጊዜ ውስጥ መጓዝ አይቻልም ።
ሳይንቲስቶችና ቴክኖሎጂስቶች ጊዜን በሰዓት ለመለካት ብዙ ጥረት አድርገዋል። ይህ ጥረት ለከዋክብት ጥናትና ለተለያዩ ያለም ዙሪያ ጉዞወች እንደመነሳሻ ረድቷል። በቋሚ መንገድ እራሳቸውን የሚደጋግሙ ክስተቶች/ኩነቶች ከጥንት ጀምሮ ጊዜን ለመልካት አገልግለዋል። ለምሳሌ ጸሃይ በሰማይ ላይ የምታደርገው ጉዞ (ቀን)፣ የጨረቃ ቅርጾች(ወር)፣ የወቅቶች መፈራረቅ(ዓመት)፣ የፔንዱለም መወዛወዝ (ሰኮንድ) ወዘተ...ይገኙበታል። በአሁኑ ጊዜ ሰኮንድ የምትለካው የሴሲየም አረር ሲወራጭ በሚያሳየው ቋሚ ድግግሞሽ ነው።
ሬይ ከሚንግ የተባለው ልብ ወለድ ጸሃፊ በ1920 ስለ ጊዜ ሲጽፍ " ሁሉ ነገር በአንድ ጊዜ እንዳይፈጸም የሚያደርገው ነገር....ጊዜ ነው " በማለት እስካሁን ድረስ ታዋቂ የሆነችውን ጥቅስ መዝግቦ አልፏል,[6] ይቺ አባባል በብዙ ሳይንቲስቶችም ስትስተጋባ ተሰምታለች፣ ለምሳሌ በኦቨርቤክ,[7] እና ጆን ዊለር.[8][9]