አሰልበርህት
From Wikipedia, the free encyclopedia
አሰልበርህት (552 -608 ዓ.ም.) ከ572 ወይም 582 ዓ.ም. አካባቢ እስከ 608 ዓ.ም. ድረስ የኬንት ንጉሥ ነበረ። ከእንግሊዝ ንገስታትም መጀመርያው የተጠመቀ እሱ ነበር። ስለዚህ በሮማ ካቶሊክ፣ በምሥራቅ ኦርቶዶክስና በአንግሊካን ሃይማኖቶች «ቅዱስ» ይባላል።
በአንግሎ-ሳክሶን ዜና መዋዕል ዘንድ፣ እሱ አባቱን የኬንት ንጉሥ ኤዮርመንሪክን ተከተለ። የፍራንኮች ንጉሥ ቻሪበርት ልጅ ቤርታን አገባት። እሷ ክሪስቲያን ነበረችና ከዚህ የተነሣ ንጉሥ ተጠምቆ ክርስትና በእንግሊዝ ሕዝብ መካከል ይፋዊ ሆነ። አውግስጢኖስ ዘካንተርቡሪ ከሮማ በ589 ዓ.ም. ተልከው የእንግሊዝ ሕዝብ መጀመርያ ሊቀ ጳጳስ ሆኑ።
አሰልበርህት ከኬንት በላይ በዘመኑ መጨረሻ በሌሎች የእንግሊዝ ደሴት መንግሥታት በኤሴክስና ምሥራቅ ኤንግላ ላይ ገዥነት ነበረው። በእርሱ ተጽእኖ የኤሴክስ ንጉሥ ሳበርህት እና የምስራቅ ኤንግላ ንጉስ ራድዋልድ በ596 ዓም ግድም ተጠመቁ።
በተጨማሪ በ594 ዓ.ም. ንጉሥ አሰልበርህት ለአገሩ ሕገ መንግሥት አወጣ። ይህ ሕገ መንግሥት በሮማይስጥ ሳይሆን የተጻፈው በጥንታዊ እንግሊዝኛ ነበረ። በኋላ ዘመን የእንግሊዝ ንጉሥ ታላቁ አልፍሬድ ከዚህ ሕገ መንግሥት ወስደው የተሻሸለ ሕገ መንግሥት አወጡ።
አሰልበርህት በ608 ዓ.ም. ካረፈ በኋላ ልጁ ኤድባልድ ተከተለው። ኤድባልድ ግን በመጀመርያ ወደ አረመኔነት ቢመልስም በኋላ ግን ክሪስቲያን ንጉሥ ሆነ።